ምናባዊ ጨዋታ ከማሂና ከኤዶም ጋር ‪#‎InMorethan90Words‬


እቴ'ሜቴ የፍትህ ጣዕም የፍቅር ሽታ፣
ቅኔሽ ያልገባው ያሰረሽ ሎሌ ምን አለሽ ማታ?
***
"ኧረ ብዙ ብዙ ነው ያለኝ፣
ከየት ጀምሬ ስንቱን ልንገርህ
እንዲያው ቢቀለኝ?"
ኧረ ንገሪኝ አንቺ የእውነት ቀለም
አንቺ የእውነት ፀዳል፣
ምንም ባያምን ፡ አይሰማው የለ
ያደለን ጆሮ ፣ መች ከቶ ይሞላል።
***
"አገሬን ብዬ ወገኔን ብዬ ከዜጎች ማዕድ
ከስፍራው ብገኝ፣
በቅጥፈት ዶሴ ችሎት ሰይሞ ወህኒ ዶለኝ።
ሀገሬ አድማስ ላይ እውነት ታስራ ፍትህ ጎድሎ
ፍትህ ጎድሎ፣
ወገን ተክዟል በጨካኝ በትር ልቡ ዝሎ
ልቡ ዝሎ፣
ህመሙ ያማል ጩኸቱ ይሰማል ወዲያ ርቆ
ወዲያ ርቆ፣
ከነጎድጓድ ድምፅ በእጥፍ ደምቆ
በእጥፍ ደምቆ።"
***
እኔን ይመመኝ ይመመኝ፣
እንባሽን አባሽ ሳቅሽን መላሽ ያድርገኝ
ያድርገኝ፣
የጠጣሽውን የእውነትን ጽዋ ያስጠጣኝ
ያስጠጣኝ።
የእውነት ጽዋ መራራ ነው
መራራ ነው፣
መፍለቂያ ምንጩ የህሊና ተራራ ነው
ተራራ ነው።
ተራራ ልወጣ ማዶ ልሻገር ላልመለስ
ላልመለስ፣
ያገሬ ልጆች በሞሉበት
በቁንጫ ቄስ ከሚቀደስ
ከሚቀደስ።
መርዙን ላስተፋው ያንን ክፉ
ያንን ክፉ፣
ንቅሳቱ በሚያታልል መንታ ምላስ ወገኖቼ እንዳይጠፉ
እንዳይጠፉ።
የአዞ እንባ ከሚያነባ ልጠብቅሽ
ልጠብቅሽ፣
ለከፈልሽው ውድ ዋጋ ምኔን ልስጥሽ
ምኔን ልስጥሽ??
ሐምሌ 16/2006 ማንችስተር ከተማ ሀገረ እንግሊዝ

No comments:

Post a Comment