ስንት ያየሁብሽ ጋዜጣ ሂዎቴ… …ብሎ ማንጎራጎር አሁን ነው። (ከ-ማስረሻ ማሞ)


ተስፋለም ጓደኛዬ እና የሥራ ባልደረባዬ ነው። ጋዜጠኛ ጥራ ስባል ቁጥር አንድ ላይ የማስቀምጠው ተስፍሽን ነው። ተስፍሽን አንድም ቀን "አንተ" ብዬ ጠርቼው አላውቅም። አንተ ብዬ ስጠራው ያራቅኹት ይመስለኛል። በስስት የማየው ታናሽ ወንድሜ ነው። ከጋዜጠኝነት እና ከጸሐፊነት ጋራ ብዙዎች ወደ እስር ቤት ሊላኩ እንደሚችሉ እገምታለሁ፤ መቼም ቀን ግን ወደ እስር ቤት ይሄዳል ብዬ የማላስበው እና በምናቤም የማይመጣልኝ ብቸኛ ሰው ቢኖር ተስፋለም ነው።
ተስፋለም የግል ፖለቲካዊ አመለካከቱ ከጋዜጠኝቱ ጋራ እንዳይጋጭበት የሚጠነቀቅ ወጣት ነው። ለጋዜጠኝነት ከፍ ያለ ክብር እና ዋጋ ይሰጣል። አንዳንዴ እቀናበታለሁ። ስለ ሚዛናዊነት፣ ስለ ተገቢነትና ስለ እውነተኛ ዘገባ አብዝቶ ይጨነቃል። ማንኛውም ዐይነት ዘገባ ከትክክለኛው ወንዝ ተቀድቶ እንዲፈስ ይመኛል፤ ያደርጋል፤ ይጓዛል። መጀመርያ ለሞያው ታማኝ መኾንን ያስቀድማል። ከተስፋለም ጋራ ሳወራ ከታናሽ ወንድሜ ጋራ የማወራ የማይመስለኝ ጊዜ አለ። ኢሕአዴግ እንደ ተስፋለም መስመራቸውን ጠብቀው ለሚሠሩ ሰዎች የማይመለስ አውሬ ይኾናል ብዬ አስቤ አላውቅም። አሁንም መታሰሩን ማመን እውነት አልመስልህ ብሎኛል! የሚሰማኝ፣ እልህ፣ ቁጭት፣ ተስፋ ቢስነትና ቁጣ ነው። እኔ እስከማውቀው ድረስ ተስፋለም የማንም ወገን አይደለም። ብቻውን በራሱ የቆመ ጋዜጠኛ ነው። ኢሕአዴግ ተቋም እንደሚፈራ አውቃለሁ። ግሩፕ በእንጭጩ ለመቅጨት የሚያክለው እንደሌለም ይገባኛል። በገለልተኝነት እንደ ተስፋለም የሚቆሙ ጋዜጠኞችንም እንደማይፈልግ የተረዳሁት ግን ዛሬ ነው።
መታሰርህ የኢሕአዴግን እብደት ቁልጭ አድርጎ አሳየኝ፤ እስር ቤት ሄደህ ሰው ስትጠይቅ እንጂ፤ አንተ ታሳሪ ኾነህ ስትጠየቅ ማየትህ ያመኛል። ይኼን ከማይ እና ከምሰማ ምነው ወይ ቀድሜ ወይ ዘግይቼ በተወለድሁ! (ከ-ማስረሻ ማሞ)

No comments:

Post a Comment