ለዘጠና ቀናት እስር ዘጠና ቃል ይበቃዋልን… ? ”ስልጣኔንም ሆነ ሰይጣኔን ሊያስለቅቅ የሚተጋ እርሱ አሸባሪ ነው” ኢህአዴግ በአበበ ቶላ ፈይሳ

#‎in90words‬ እናስባቸው ዘንድ ዞን ዘጠኞች በእስር ቤት እንደተቆለፈባቸው ዘጠና ቀን የፊታችን ሃሙስ ይሞላቸዋል። በፊት በማዕከላዊ ያለ ክስ ያለ ፍርድ ታስረው የነበሩት እጅግ ወዳጆቻችን የሆኑት ዞን ዘጠኞች አሁን ከዚህ መልስ ኦነግ ከዚህ መልስ ግንቦት ሰባት ብዬሃለሁ ብለው የሽብረተኝነት ክስ መስርተውባቸዋል። በአሁኑ ሰዓት ወንዶቹ ቂሊጦ ሴቶቹ ቃሊቲ ይገኛሉ።
ለመሆኑ እነዚህ ልጆች የምር አሸባሪ ሆነው ነው ያታሰሩትን ብለን የጠየቅን እንደሆነ መለሱ አዎ ነው። ማንን አሸበሩ ብሎ ተከታይ ጥያቄ መጠየቅ ታድያ ተገቢ ነው፤ ማንን አሸበሩ… ያሸበሩት በሆነው ባልሆነው የምተሸበረውን ኢህአዴግ ን ነው። ምን ብለው አሸበሯት ብሎ የሚጠይቅ ካለም ”ህገ መንግስቱ ይከበር” እና ”ሰለሚያገባን እንናገራልን” የሚሉት አቋማቸው ናቸው ኢህአዴግን ያሸበሯት። ድመት የገደለ እጅ ዝም ብሎ ይንቀጠቀጣል እንደሚሉት አባባል ሆኖ እንጂ ሀገ መንግስቱ ይከበር ማለት እና ስለሚያገባን ዝም አንልም እንናገራለን እንገማገማለን ማለት የሚያሸብር ነገር ሆኖ አየደለም ኢህአዴግ ”የተነጰረጰረችው” መንጰርጰር/ ጰርጳራ የምትለው ቃል መነሻዋ የት እንደሆነ ባላውቅም አባቴ እጅግ ለሚፈራ ሰው ይሸልማት የነበረች ቃል ናት።
ጉምቱዋ ኢህአዴግ በአንድ ፍሬዎቹ ዞን ዘጠኞች ለምን ተንጰረጳረች ብለን የጠየቅን እንደሆነ የመጀመሪያው መላ ምት ”እኛ ሰባት ሆነን ጀመረን የ አስራ ሰባት አመቱን ደርግ ከደመሰስን እነዚህ ደግሞ ዘጠኝ ሆነው ተደራጅተው ሃያ ዘጠኝ አመት ሳይሞላን በእንጭጩ ሊያስቀሩን ነው” የሚል ፍርሃት ሊሆን እንደሚችል ይጠረጠራል።
እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ዞን ዘጠኞችን መንግስት ለመደምሰስ ቀርቶ ካሴት ለመደምሰስም ተነሳሽነቱ አልነበራቸውም። ”ስለሚያገባን እንጦምራለን” ማለት ወይም ሀገ መንግስቱ ይከበር ማለት ስልጣን ልቀቁ ማለት አይደለም። እንደ ዞን ዘጠኞች ውትወታ ኢህአዴግ ስልጣን ባይለቅም ሰይጣኑ ከለቀቀው ግድ ያላቸው አይደሉም።
ኢህአዴግስ ምን አለች፤ ያሉ እንደሆነ ስልጣኔንም ሆነ ሰይጣኔን ሊያስለቅቅ የሚተጋ እርሱ አሸባሪ ነው አለች፤
ጰርጳራ በሏት!
እና እላችኋለሁ ዘጠና ቀናት በእስር ያሳልፉትን ዞን ዘጠኞች #in90words ላስባቸው አልኩና አልበቃህ አለኝ፤ ይሄኔም ያንን የአማርኛ ቋንቋ ተማሪ አስታውስኩት፤
መመህሩ እስቲ ሀገራችሁን በስድስት መስመር ግጥም ገለጹ ብሎ የከፍል ስራ ሰጠ፤ ወድያውም አንዱ ተማሪ ጨርሻለሁ አለ፤ እስቲ አንበበው ሲባል፤
እንኳን ስድስት መስመር መቶም አይበቃሽ
እንደው በደፈናው የጉድ ሀገር ነሽ
ብሎ በሁለት መስመር ጨረሰው።
እናም ወዳጆቼ ዞን ዘጠኞች እና ሌሎችም ጋዜጠኞች የሃይማኖት መብት ተከራካሪዎች ፖለቲከኞች እና ያገባኛል ባዮች ሰለ እናነት #in90words ተገለጾ የሚያልቅ ነገር የለም።

No comments:

Post a Comment